አርባ ምንጭ፡ ታህሳስ 27/2018 ዓ/ም (አርባ ምንጭ ከተማ መ/ኮ)
የአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ አብነት ተስፋዬ ፀሐይ ጎልጎታ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት በአርባምንጭ ከተማ በማህበራዊ እና በልማታዊ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ለልማት ሆነ ለተቸገሩ ፈጥኖ ደራሽ መሆኑን ተናግረዋል። በከተማው የሚገኙ የግል ባለሀብቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አቅመ ደካማዎችንና ሌሎች ድጋፍ በሚሹ ጉዳዮች ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ፀሐይ ጎልጎታ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀሐይ አካሉ ድርጅቱ ያለምንም ክፍያ በነጻ 30 ህጻናትን የዓመቱን ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፍን ለ2ኛ ዙር በቅድመ መደበኛ እያስተማረ እንደሚገኝ ገልፀው በዛሬው ዕለት የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ህፃናት ማዕድ ማጋራቱን ተናግረዋል። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በከተማው ጧሪ ላጡ፣ ደጋፊና ተንከባካቢ የሌላቸውን በመለየት አልባሳትን ጨምሮ መሰል አስቤዛና ለበዓል መዋያ እያጋራ መቆየቱን አስረድተዋል።
በተጨማሪ በከተማው በሚሰሩ ልማቶች የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መቆየቱን አውስተው በተለያዩ ማህበራዊ መሠረት ውስጥ ላሉ ሴቶችና ሕፃናት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መቆየቱን ተናግረዋል። ድርጅቱ ቀጣይ በተለያየ መልክ የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ወ/ሮ ፀሐይ ገልጸዋል። በመርሃግብሩ ላይ ፀሐይ ጎልጎታ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀሐይ አካሉ ጨምሮ የአርባምንጭ ከተማ አመራሮችና ሌሎች ተገኝተዋል።

